2 Chronicles 35

ኢዮስያስ ፋሲካን ማክበሩ

35፥1፡18-19 ተጓ ምብ – 2ነገ 23፥21-23 1ኢዮስያስ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ፋሲካን አደረገ፤ በመጀመሪያውም ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካው በግ ታረደ። 2ካህናቱን በየአገልግሎታቸው መደበ፤ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገልግሎትም እንዲተጉ አበረታታቸው። 3እስራኤልን ሁሉ ያስተምሩ ለነበሩትና ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ለቀደሱት ሌዋውያን እንዲህ አላቸው፤ “የእግዚአብሔርን ታቦት የዳዊት ልጅ ሰሎሞን ባሠራው ቤተ መቅደስ አኑሩ፤ በእናንተ ትከሻ አትሸከሙት፤ አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርንና ሕዝቡን እስራኤልን አገልግሉ። 4በእስራኤል ንጉሥ በዳዊትና በልጁ በሰሎሞን በተጻፈው መመሪያ መሠረት፣ እንደየቤተ ሰባችሁ በክፍል በክፍላችሁ ራሳችሁን አዘጋጁ።

5“ሌዋውያን ባልሆኑ ወንድሞቻችሁ አንጻር እንደየቤተ ሰቡ ምድብ በተቀደሰው ስፍራ ቁሙ፤ ለእያንዳንዱም የቤተ ሰብ ምድብ ሌዋውያን ይኑሩት። 6ከዚያም የፋሲካውን በጎች ዕረዱ፤ ራሳችሁን ቀድሱ፤ እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ባዘዘውም መሠረት ዕርዶቹን ለወንድሞቻችሁ አዘጋጁ።”

7ኢዮስያስም እዚያ ለነበሩት ሕዝብ ሁሉ ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆኑ በአጠቃላይ ሠላሳ ሺሕ በግና ፍየል እንዲሁም ሦስት ሺሕ ወይፈን ከራሱ ሀብት ሰጠ።

8ሹማምቱም ለሕዝቡ፣ ለካህናቱና ለሌዋውያኑ በገዛ ፈቃዳቸው አዋጥተው ሰጡ። የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አለቆች የሆኑት ኬልቅያስ፣ ዘካርያስና ይሒኤልም ለፋሲካ መሥዋዕት የሚቀርቡ ሁለት ሺሕ ስድስት መቶ በግ እንዲሁም ሦስት መቶ ወይፈን ሰጡ። 9ደግሞም ኮናንያ፣ ወንድሞቹ ሸማያና ናትናኤል እንደዚሁም የሌዋውያኑ መሪዎች ሐሸቢያ፣ ይዔኤልና ዮዛባት ለፋሲካ መሥዋዕት እንዲሆኑ አምስት ሺሕ በግና ፍየል አምስት መቶም በሬ ለሌዋውያኑ ሰጧቸው።

10የአገልግሎቱ ዝግጅት በተጠናቀቀ ጊዜ፣ ንጉሡ ባዘዘው መሠረት ካህናቱ በየክፍላቸው ከተመደቡት ሌዋውያን ጋር ቦታ ቦታቸውን ይዘው ቆሙ። 11የፋሲካው በጎች ታረዱ፤ ካህናቱ የተቀበሉትን ደም ረጩ፤ ሌዋውያኑም የበጎቹን ቈዳ ገፈፉ። 12በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈው ለእግዚአብሔር እንዲያቀርቡም፣ እንደየቤተ ሰቡና እንደየምድቡ ለሕዝቡ ለመስጠት የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለዩ፤ ወይፈኖቹንም እንደዚሁ አደረጉ። 13እነርሱም የፋሲካውን መሥዋዕት በሥርዐቱ መሠረት ጠበሱ፤ የተቀደሰውንም ቍርባን በምንቸት፣ በሰታቴና በድስት ቀቀሉ፤ ወዲያውኑም ለሕዝቡ አደሉ። 14ከዚህ በኋላ ለራሳቸውና ለካህናቱ ዝግጅት አደረጉ፤ ምክንያቱም ካህናቱ የአሮን ልጆች የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሥቡን እስከ ሌሊት ድረስ ያቀርቡ ስለ ነበር ነው። ስለዚህ ሌዋውያኑ ለራሳቸውና ለካህናቱ ለአሮን ልጆች ዝግጅት አደረጉ።

15መዘምራኑ የአሳፍ ዘሮች በዳዊት፣ በአሳፍ፣ በኤማንና በንጉሡ ባለ ራእይ በኤዶታም በተሰጠው መመሪያ መሠረት በቦታቸው ነበሩ። በእያንዳንዱ በር ላይ የነበሩት በር ጠባቂዎችም ሌዋውያን ወገኖቻቸው ስላዘጋጁላቸው፣ ከጥበቃ ቦታቸው መለየት አያስፈልጋቸውም ነበር።

16በዚህ ዐይነት የፋሲካን በዓል በማክበርና የሚቃጠል መሥዋዕት በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ በማቅረብ የእግዚአብሔር አገልግሎት ሁሉ ንጉሥ ኢዮስያስ ባዘዘው መሠረት በዚያኑ ቀን ተከናወነ። 17በዚያን ጊዜ በስፍራው የተገኙ እስራኤላውያን የፋሲካን በዓል አከበሩ፤ የቂጣንም በዓል እንደዚሁ ሰባት ቀን አከበሩ። 18ከነቢዩ ከሳሙኤል ዘመን ወዲህ እንዲህ ያለ ፋሲካ በእስራኤል ዘንድ ተከብሮ አያውቅም፤ ኢዮስያስ ከካህናቱ፣ ከሌዋውያኑ፣ ከመላው ይሁዳና ከእስራኤል፣ በዚያ ከነበሩትም ከኢየሩሳሌም ሰዎች ጋር እንዳከበረው አድርጎ ያከበረ አንድም የእስራኤል ንጉሥ የለም። 19ይህ ፋሲካ የተከበረው በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት በዐሥራ ስምንኛው ዓመት ነበር።

የኢዮስያስ መሞት

35፥20–36፥1 ተጓ ምብ – 2ነገ 23፥28-30 20ከዚህ ሁሉ በኋላ ኢዮስያስ ቤተ መቅደሱን አደራጅቶ ባጠናቀቀ ጊዜ፣ የግብፅ ንጉሥ ኒካዑ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ፣ በከርከሚሽ ላይ ለመዋጋት ወጣ፤ ኢዮስያስም ጦርነት ሊገጥመው ወጣ። 21ኒካዑ ግን፣ “የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፤ አንተንና እኔን የሚያጣላን ምንድን ነው? ጦርነት ከገጠምሁት ቤት ጋር እንጂ በአሁኑ ጊዜ አንተን የምወጋህ አይደለሁም፤ እግዚአብሔር እንድፈጥን አዝዞኛል፤ ስለዚህ ከእኔ ጋር ያለውን እግዚአብሔርን መቃወምህን ተው፤ አለዚያ ያጠፋሃል” አለው።

22ኢዮስያስ ግን ሌላ ሰው መስሎ በጦርነት ሊገጥመው ወጣ እንጂ ወደ ኋላ አልተመለሰም፤ በመጊዶ ሜዳ ላይ ሊዋጋው ሄደ እንጂ፣ ኒካዑ ከእግዚአብሔር ታዝዞ የነገረውን ሊሰማ አልፈለገም።

23ቀስተኞች ንጉሥ ኢዮስያስን ወጉት፤ እርሱም የጦር መኰንኖቹን፣ “ክፉኛ ቈስያለሁና ከዚህ አውጡኝ” አላቸው። 24ስለዚህ ከሠረገላው አውርደው በራሱ ሠረገላ ላይ አስቀምጠውት ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት፤ እዚያም ሞተ፤ በአባቶቹ መካነ መቃብር ተቀበረ፤ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሁሉ አለቀሱለት።

25ኤርምያስ ለኢዮስያስ የሐዘን እንጕርጕሮ ግጥም ጻፈለት፤ ወንዶችና ሴቶች ሙሾ አውራጆች ሁሉ እስከ ዛሬ ድረስ በዚህ ግጥም ኢዮስያስን ያስታውሱታል፤ ይህም በእስራኤል የተለመደ ሆኖ በልቅሶ ግጥም መጽሐፍ ተጽፏል።

26በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ድርጊትና በእግዚአብሔር የሕግ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት ያከናወነው መንፈሳዊ ተግባር፣ 27ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ያደረገው ሁሉ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፏል።

Copyright information for AmhNASV